በዚህ መፅሐፍ ውስጥ የምናገኛቸው ፈላስፎች እና የፖለቲካ እሳቤዎቻቸው ዓለም እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሷ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ናቸው። ለሰው ልጅ የአኗኗር ሁናቴ የተሻለ መንገድ ለማሳየትና ለመቀየስ የጣሩ፣ በጥረታቸውም አያሌ ሕዝቦችን ከጨለማ ያወጡ፣ በእሳቤዎቻቸውም ከግለሰብ ባሻገር የሀገራትን ህልውና ያቀኑ ናቸው።
ምን ዓይነት የህብረተሰብ አደረጃጀት ይበጃል? የመንግሥት መኖር ጥቅም ምንድነው? ይኑር ከተባለስ ምን ዓይነት መንግሥትና የመንግሥት ሥርዓት ይሻላል? የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባሕሪይስ ለአጠቃላዩ የህብረተሰብ አደረጃጀት ምን ሚና ይጫወታል? የመንግሥትነት ሥልጣን ከእግዚአብሔር የተሰጠ ነውን? ወይንስ በሕዝቦች ስምምነት የተፈጠረ? መንግሥት ጨቋኝ የሚሆነው በተፈጥሮው የተነሳ ነው፣ ወይስ ለጠቅላላው ጥቅም በሚል ግብ? ለአምባገነን የተመቸ ሕዝብ አለን? የግለሰብ መብትስ እስከምን ድረስ ነው? እነዚህን እና ሌሎች መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት ትውልዶችን ያነጋገሩ እሳቤዎችን አፍልቀዋል።
ለመጽሐፉ “ሁነኛውን ማኅበራዊ ውል ፍለጋ” የተሰኘ ርዕስ የተሰጠበት ምክንያት፣ አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ፍልስፍና እሳቤዎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ለሰው ልጆች የተሻለውን ማኅበራዊ ውል (Social Contract) ከመጠቆም ወይም ይዘቱን እና አተገባበሩን ከማብራራት ጋር ዝምድና ስላላቸው ነው። በርግጥ ከማኅበራዊ ውል ጋር በተያያዘ ብዙውን ጊዜ ስማቸው የሚጠቀሰው እንደ ቶማስ ሆፕስ፣ ጆን ሎክ እና ሩሶ ያሉት ፈላስፎች ናቸው፤ መጽሐፉ የእነሱንም እሳቤዎች አካትቷል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከግለሰብ እስከ ቡድን መብት/ኃላፊነት፣ ከጋራ ጥቅም እስከ ማኅበራዊ ውል፣ ከመንግሥት ባሕሪይ እና አስፈላጊነቱ፣ እንዲሁም ለዜጎችም ሆነ ለመንግሥት ሊበጁ እስከሚገቡ ገደቦችና ሌሎች አያሌ የፖለቲካ እና የአስተዳደር እሳቤዎች ተተንትነዋል። ለፖለቲከኞች፣ ለፀሐፍት፣ እንዲሁም ሀገር እና ፖለቲካ ግድ ለሚላቸው ሁሉ — ከላይ ከላይ ሳይሆን ከጽንሰ-ሀሳብ አንስቶ መረዳትን ለሚሹ ሁሉ — ጥሩ ግብዓት እንደሚሆን አምናለሁ። መልካም ንባብ።